መልካ ኢትዮጵያ በወረኢሉ ወረዳ 04፣ 06 እና 011 ቀበሌዎች ከሚሰራቸዉ ስራዎች መካከል አንዱ የአፈርና ዉሀ ጥበቃ ስራዎችን ሲሆን በወረዳዉ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ቦረቦሮች ይገኛሉ ከእነርሱም መካከል በቀበሌ 011 አካባቢ የነበረዉ ቦረቦርን ለአብነት ያክል ማንሳት ይቻላል፡፡

በ011 ቀበሌ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት እና በአካባቢያቸዉ የተፋሰስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደርብ ሀሰን የአፈርና ዉሀ ጥበቃ ስራዉ ከመሰራቱ በፊት ጎረጎር የነበረዉን ቦታ ሲገልፁት “የአፈርና ዉሀ ጥበቃ ስራዉ ከመሰራቱ በፊት ይሄ ቦታ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ በፊት የነበረዉ ቦረቦር (ሸለቆ) ስለማያራምድ የአንድ አካባቢዉ ማህበረሰብ ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ ሰዉ ሲሞት ቀብር እንኳን ለመቅበር ቦረቦሩ ስለማያሳልፍ አንችልም ነበር፡፡”
የኮሚቴዉ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደርብ የተፋሰስ ስራዉ አጀማመሩ እንዴት እንደነበር ሲናገሩ “መልካ-ኢትዮጵያ ወደ አካባቢያችን መጥቶ ይህንን ቦታ እንድናለማላችሁ ፈቃደኛ ናችሁ ወይ ብሎ ጠየቀን እኛም ፈቃደኛነታችንን በደስታ ገልፀን፡፡ አካባቢዉ ከለማ ቡኋላ የከብት ግጦሽ ክልክል መሆኑን ተስማምተን ስራዉን በከፍተኛ ጥረት በመስራታችን ቦታዉ አሁን የተሻለ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሎዋል፡፡”

አቶ ደርብ ሀሰን በመጨረሻም “መልካ- ኢትዮጵያ አስቸጋሪ የነበረዉን ቦረቦር ወደ ነበረበት ለመመለስ የአካባቢዉን ማህበረሰብ በማስተባበር እንጨት፣ ጋቢዮን፣ ችግኞችን እና ድንጋይ በማቅረብ የአካባቢዉ ማህበረሰብ በጉልበቱ ታግሎ የቦረቦሩን ችግር ለመቅረፍ ተችሏል፡፡ ይሄ የተሰራዉ ስራ ተጠብቆ እንዲቆይ የተፋሰስ ኮሚቴዉ የዉስጥ ደንብ አዉጥቶ በአገገመዉ አካባቢ ላይ የተከለከሉ ነገሮችን ያደረገ የአካባቢዉ ነዋሪ ቅጣት እንዲጣልበት በማድረግ የተፋሰሱን ቦታ እየጠበቅነዉ እንገኛለን፡፡” በማለት ሀሳባቸዉን ቋጭተዋል፡፡
አቶ ሱለሂማን ሀሰን በወረኢሉ ወረዳ አባቀሬ መንደር ቀበሌ 011 ዉስጥ ነዋሪ ሲሆኑ በአካባቢያቸዉ የተፋሰስ ኮሚቴዉ ምክትል ሰብሳቢ እና ገንዘብ ያዥ ናቸዉ፡፡ በቀበሌ 011 አባቀሬ መንደር ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ በመልካ ኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተሰራዉ የአፈርና ዉሀ ጥበቃ ስራ 0.5 ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን 850 ሜትር ርዝማኔ አለዉ፡፡ አቶ ሱለሂማን በአካባቢያቸዉ የሚገኘዉ ለበርካታ ጊዜያት የተቸገሩበት ቦረቦር በ2011ዓ.ም ከመሰራቱ በፊት ምን እንደሚመስል ሲናገሩ “ይሄ አካባቢ ቀድሞ በጣም የተቦረቦረ አካባቢ ነበር ከሰዉ ቁመት በሚበልጥ ርዝመት መሬቱ በጣም ተቦርቡሮ ነበር፡፡ወደ ቦረቦሩ ከብቶች ከገቡብን እነርሱን ለማዉጣት ከፍተኛ ስቃይ ነበር፡፡ በክረምት ወቅት ቦረቦሩን ለመሻገር ባህር ዛፎችን እየቆረጥን በቦረቦሩ ላይ በማድረግ ሰዎች እና ከብቶቻችን በጊዜያዊነት ለማሻገር እንጥር ነበር፡፡”

አቶ ሱለሂማን በመቀጠልም “ሆኖም ግን መልካ ኢትዮጵያ ወደ መንደራችን ከመጣ ቡኋላ የአፈርና ዉሀ ጥበቃ ስራዉን መስራት ችለናል የቦረቦር ስራዉ ከተሰራ በኋላ አርሶ አደሩ እና የአካባቢዉ ማህበረሰብ እፎይ ብሏል ክረምት መጣ በጋ ሆነ መሬቱ ሰላም ሆኖዋል፡፡” “የቦረቦር ስራዉን ለመጨረስ አራት ወራት የወሰደ ሲሆን የአካባቢዉ ማህበረሰብ በጉልበቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ መልካ ኢትዬጵያ ደግሞ ጋቢዮን፣ ድንጋይ፣ እንጨት እንዲሁም የተለያዩ የዘር ችግኞችን በማቅረብ የቦረቦር ስራዉ እንዲሰራ ደግፏል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ መልካ ኢትዮጵያ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሳላመሰግነዉ አላልፍም” ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ሱለሂማን “የአካባቢዉ ማህበረሰብም የተፋሰስ መሬቱ መልሶ እንዳይቦረቦር እና ወደ ቀድሞ ይዞታዉ እንዳይመለስ የተዋቀረዉ ኮሚቴ ህግና ደንብ በማዉጣት እንዲሁም በእንጨት ቦታዉን በማጠር በመንከባከብ እና በመጠበቅ ላይ እንገኛለን፡፡” በማለት ሃሳባቸዉን አጠቃለዋል፡፡