MELCA-Ethiopia

MELCA-Ethiopia Logo

መልካ ኢትዮጵያ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ በሶስት ቀበሌዎች ዉስጥ (011፣ 06፣ 04) “የገጠር ኑሮን ማሻሻል ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮጀክት ቀርፆ ከብሬድ ፎር ዘ ዎርልድ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከነሐሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ዓላማ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ሲሆን ፕሮጀክቱ ሁለት መሰረታዊ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አንዱ የአግሮ-ኢኮሎጂ (ስነ ምህዳሪያዊ ግብርና) ተግባራትን በማስተዋወቅ የአፈርና ዉሀ ጥበቃን በመስራት፣ ነባር ሀገር በቀል የሆኑ ዝርያዎችን ከጥፋት በመታደግ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ተፈጥሮአዊ የሆኑ ማዳበሪያዎችን በማስተዋወቅ የተፈጥሮ ሀብታቸውን በዘላቂነት እንዲጠብቁ እና ጥቅም ላይ እንዲዉሉ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተግባራዊ የሚያደርግ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ የኑሮ ማሻሻያና የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በመመስረት የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ የሚያተኩር ድጋፍ ማድረግ ነዉ፡፡

እንደልቤ የነባር ዘር ማህበር በ2011ዓ.ም እየጠፉ ያሉ ነባር ሀገር በቀል ዘሮችን ለማቆየት እና ለማባዛት በወረኢሉ ወረዳ 06 ቀበሌ ፈቃደኛነታቸዉን ባሳዩ 72 አርሶ አደሮች በ2011ዓ.ም የተመሰረተ ነዉ፡፡ ከአባላቱ ዉስጥም 24 ሴት አርሶ አደሮች እና 48 ወንድ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡

የእንደልቤ የነባር ዘር ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ሞዴል አርሶ አደር ጥላሁን አበበ ስለ ማህበሩ አመሰራረት ሲናገሩ “ይህን ማህበር ልንመሰርት የቻልነዉ እየጠፉ ያሉ ሀገር በቀል የሆኑ የነባር ዘሮችን ለማሰባሰብ እና ወደ ምርት ለማስገባት ነዉ፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የነባር ዘሮቹን ጠብቀዉ ካቆዩ አርሶ አደሮች እና በአካባቢያችን ዙሪያ ከሚገኙ አካባቢ ገበያዎች ከመልካ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን 8 ነባር የጤፍ እና የስንዴ ዘሮችን በ27,173 ብር በማሰባሰብ በ2012 ዓ.ም የማህበሩ አባላት ነባር ዘሮቹን በእርሻ መሬቶቻቸዉ ላይ እንዲዘሩ አድርገናል፡፡” ሲሉ ስለ ማህበሩ ተግባር ገልፀዋል፡፡

የእንደልቤ የነባር ዘር ማህበር ሰብሳቢ ሞዴል አርሶ አደር ጥላሁን አበበ በ2012 ዓ.ም የዘሩትን ነባር ሀገር በቀል የስንዴ ዘር ምርት በመሰብሰብ ላይ

በመቀጠልም አቶ ጥላሁን “ማህበራችን ለአባላቱ ከተሰበሰቡተት የነባር ዘሮች ከ10ኪ.ግ እስከ 20ኪ.ግ እንደየ መሬታቸዉ መጠን አከፋፍሏል፡፡ በ2012 ዓ.ም አባላቱ በየማሳዎቻችን ላይ እነዚህን ነባር ዝርያዎች ዘርተናል፣ እያባዛንም እንገኛለን፡፡ ምርቶቹ ከደረሱ ቡኋላ ዘሮቹን በማባዛት ከማህበሩ ከወሰድነዉ የዘር መጠን ላይ አንድ ኪ.ግ በመጨመር ተመላሽ እናደርጋለን፡፡ እስከአሁንም ባለዉ ጊዜ ነባር ዘሮቹ ከመሬቶቻችን ጋር በጣም ተስማምተዋል፡፡ በተለየ ደግሞ ተፈጥሮዊ በሆነ ማዳበሪ የተዘሩት ነባር ዘሮች ዉጤታቸዉ የሚያረካ ነዉ፡፡” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም አቶ ጥላሁን ስለ መልካ ኢትዮጵያ ድጋፍ ሲናገሩ “መልካ ኢትዬጵያ ወደ መንደራችን ከመጣ ቡኋላ በጣም ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል በተለይ ነባር ዘሮቹን በማቆየት እና ተፈጥሮአዊ የሆነ የማዳበሪ አዘገጃጀት ላይ ለአርሶ አደሮቻችን ሰፊ ስልጠና ሰጥቶናል፡፡ ነባር ዘሮቹ ተጠብቀዉ መቆየታቸዉ ስላለዉ ጠቀሜታ ከመልካ ኢትዬጵያ ስልጠና ስለ ነባር ዘሮቹ እህል ጥራት፣ ጣዕምና አልሚነት የበለጠ ለማወቅ ችለናል፡፡ እንዲሁም ከኛ ቀደም በዚህ ስራ የተጠቀሙ ገበሬዎች ሲገልፁልን በዚህ በመነሳሳት ነባር ዘሮቹን ለማቆየት እና ለማባዛት ቃል በመግባት ማህበሩን ልንመሰርት ችለናል፡፡ በዚህም የመልካ ኢትዮጵያ ድጋፍ ከፍተኛ ነዉ፡፡” በማለት ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡

የእንደልቤ የነባር ዘር ማህበር ሰብሳቢ ሞዴል አርሶ አደር ጥላሁን በማሳቸዉ ላይ እና በቤታቸዉ ጓሮ ላይ ያዘጋጁት ተፈጥሯዊ የሆነ ማዳበሪያ

“ማህበራችን በተመሰረተበት ቀበሌ 06 በርካታ አርሶ አደሮች የሚገኙ ሲሆን 72 የምንሆን አርሶ አደሮች ይህን ማህበር ልንመሰርት የቻልነዉ፡፡ የማህበራችን አባላት የሆኑ አርሶ አደሮች ነባር ዘሮቹን በመጠቀም እያሳዩት ያለዉን ዉጤት በማየት በቀበሌያችን የሚገኙ የማህበራችን አባላት ያልሆኑ አርሶ አደሮች ወደ ማህበራችን ለመግባት እንዲሁም ነባር ዘሮቹን በማሳዎቻቸዉ ላይ ለመዝራት ፍላጎት እንዳላቸዉ እየተናገሩ ነዉ፡፡” ሲሉ የእንደልቤ የነባር ዘር ማህበር ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ይናገራሉ፡፡

አቶ ጥላሁን በመጨረሻም “እኔ በግሌ መልካ ኢትዮጵያ ከሰጠን ስልጠና ቡኋላ ራሴን በማሳመን ነባር ዘሮቹን በማሳዬ ላይ ለመዝራት እና ተፈጥሮአዊ በሆነ ማዳበሪያ በመጠቀም ዉጤቱን ለማየት ወሰንኩኝ፡፡ ይሄንም ለማድረግ በራሴ በስልጠናዉ ባገኘሁት ተፈጥሮአዊ የሆነ ማዳበሪ አዘገጃጀት መሰረት ማዳበሪያዎችን በማዘጋጀት ለሙከራ ያክል በ2012ዓ.ም በመዝራት ዉጤቱን በማየት ላይ እገኛለሁ፡፡ የነባር ዘሮቹን በተፈጥሮዊ ማዳበሪያ በመጠቀም የዘራሁዋቸዉ ዘሮች ቀድሞ ስጠቀመዉ ከነበዉ ምርታቸዉ የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡”

 

ወ/ሮ አበቡ አሊ በማሳቸዉ ላይ ነባር ሀገር በቀል የስንዴ ዘር በመሰብሰብ ላይ

በተመሳሳይ ወይዘሮ አበቡ አሊ በ06 ቀበሌ ውስጥ በእንደልቤ ነባር ዘር ማህበር እንዲሁም በሴቶች ራስ አገዝ ቡድን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ታታሪ ሴት ናቸዉ፡፡ ወ/ሮ አበቡ ስለነባር ዘር ባገኘችዉ ስልጠና እንዲሁም ከነባር ዘር ማህበሯ 10 ኪ.ግ የስንዴ ዘር በመዉሰድ ተክላ ነበር፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ምርትዋን በመሰብሰብ ላይ ስትሆን ነባር ዘሩ እያሳየዉ ያለዉን ዉጤት በመመልከት ደስተኛ መሆኑዋን ገልፃለች፡፡