18ኛዉ የመልካ ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ
መልካ ኢትዮጵያ የማህበረሰቦችን እና የስነ-ምህዳሮን ተግዳሮቶችን የመቋቋም ማህበረሰባዊ እና አካባቢያዊ አቅም ለመገንባት እንዲሁም ባህላዊ ስርአቶቻችዉ ተጠብቀዉ እንዲቆዩ ለማድረግ በመስራት ላይ የሚገኝ እንደ አዉሮፓዉያን የዘመን አቆጣጠር በ2004 የተመሰረተ መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ነዉ፡፡
መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም መልካ ኢትዮጵያ የጠቅላላ ጉባኤ አባላቱ በተገኙበት 18ኛዉን መደበኛ የጠቅላላ ገባኤዉን አካሄዷል፡፡ በጉባኤዉ መጀመሪያም በአመቱ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ የመልካ-ኢትዮጵያ 3 አባላት ለሻምበል ገ/መድህን ቢረጋ፣ አቶ ነጋሽ ተክሉ እና አቶ ሳላህ ሁሴን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤዉ በተያዙ አጀንዳዎች መሰረት የመልካ-ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ የ2021 ኦዲት ሪፖርት በውጪ ኦዲተር የቀረበ ሲሆን ጉባኤዉም የኦዲት ሪፖርቱን መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ በተጨማሪም የ2021 አመታዊ የስራ ክንዉን አጠቃላይ ዘገባ በቦርዱ ሊቀመንበር ዶ/ር መለሰ ዳምጤ የቀረበ ሲሆን የ2021 ዓመታዊ የሥራ ክንውን ዝርዝር ዘገባ እና የ2022 የስራ እቅድና በጀት በመልካ ኢትዮጵያ ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ ቀርቧል፡፡
በዚህም መሰረት መልካ-ኢትዮጵያ በ2021 የስራ ዘመን ካቀደው ብር 43.2 ሚሊዮን ብር ውስጥ 36.1 ሚሊዮን ብር ላቀደው አላማ በአራቱ ፕሮግራሞች ማለትም በተፈጥሮ አካባቢ አስተዳደር፣ ሥነ ምህዳሪያዊ የተፈጥሮ ግብርና፣ ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆነ የገቢ ማስገኛ ሥራ እና የወጣቶች እና ህጻናት የማብቃት ፕሮግራሞችን እንዲሁም ስነ ህዝብ ጤና እና አካባቢ ፕሮግራም በአምስቱ የፕሮጀክት አካባቢዎች ስር አውሏል፡፡ ይኸውም ከእቅዱ 84% መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህም የፕሮጀክት አፈጻፀምና የአስተዳደር ህግን በጠበቀ ሁኔታ የተሰራ መሆኑ በኦዲተሮች ሪፖርት ላይ ተረጋግጧል፡፡ የድርጅቱ ሂሳብ ደረጃውን በጠበቀ የሂሳብ አሠራር የተሠራና ኢፕሳስን መጠቀሙ ፈር ቀዳጅና ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን አባላቱም አንስተዋል፡፡
የመልካ-ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2022 እቅድ ተዘጋጅቶ ለአባላት ለአስተያየት የቀረበ ሲሆን፡፡ በዘገባው መልካ-ኢትዮጵያ በ2022 በአራቱ ፕሮግራሞች ሥር ባሉ ፕሮጀክቶች እና በዋናው መ/ቤት ሊያከናውናቸው የታቀዱ ተግባራት ተመልክተዋል፡፡ በበጀት ረገድም በአጠቃላይ እ.ኤ.አ በ2022 ሊሠሩ ለታቀዱ ሥራዎች በጠቅላላ በጀት ብር 37.5 ሚሊዮን ወጪ የተዘጋጀ መሆኑን በዝርዝር ተመልክቶ አፅድቋል፡፡
በተጨማሪም ጉባኤዉ የአባልነት ጥያቄ በተመለከተ በትምህርት ዝግጅታቸውና በስራ ዘርፋቸዉ ተገቢ ስልጠና ያላቸው እና የመልካ-ኢትዮጵያን ዓላማም ለመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የአባልነት ጥያቄ ያቀረቡ አምስት አመልካቾችን በሙሉ ድምፅ የአባልነት ጥያቄያቸዉን ተቀብሏል፡፡ እንዲሁም በጎደሉ የጠቅላላ ጉባኤ እና ቦርድ አመራሮች የማሟያ ምርጫ የተደረገ ሲሆን በዚሁም መሰረት ወ/ሮ ፍቅርተ አሰፋ የጠቅላላ ጉባኤው ም/ሰብሳቢ እንዲሁም ወ/ሮ ነፃነት ገነነ የመልካ-ኢትዮጵያ የቦርድ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የመልካ-ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባኤ ም/ሰብሳቢ ሆነዉ ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አለማየሁ አያሌው ሰብሳቢ ሆነዉ እንዲገለግሉ ተመርጠዋል፡፡