መልካ ኢትዮጵያ 19ኛዉን አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤዉን አባላቱ በተገኙበት አካሄደ
ከተፈጥሮ ጋር ዘለቄታዊ ግንኙነት ያላቸዉን ባህላዊ እሴቶቻችን እንዲያንሰራሩ እና የማህበረሰብን እና የስርአተ ምህዳርን አቅምን ለማጎልበት አላማ አድርጎ በ1997ዓ.ም የተቋቋመዉ መልካ ኢትዮጵያ 19ኛዉን አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤዉን አባላቱ በተገኙበት መጋቢት 16 ቀን 2015ዓ.ም አካሂዷል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤዉ መክፈቻ መልካ-ኢትዮጵያን ከመሰረቱት መካካል የነበሩትና የጠቅላላ ጉባኤዉ የመጀመሪያ ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሄር ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው አስመልክቶ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጔል፡፡ ዶ/ር ተወልደብርሃን ከማህበሩ ጋር የነበራቸዉን ቆይታ የሚያስታዉስ አጭር የማስታወሻ የቪዲዮ ፊልምም ቀርቧል፡፡
በጉባኤዉም የመልካ-ኢትዮጵያ የ2022 እ.ኤ.አ ኦዲት ሪፖርት፣ ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት እና የ2023 የስራ እቅድና በጀት በበቦርዱ ሊ/መንበር ዶ/ር መለሰ ዳምጤ እና በማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ እንዲሁም በውጪ ኦዲተሩ በአቶ ደጀኔ ያብጌታ ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በቀረቡት ሰነዶች ላይ የጠቅላላዉ ጉባኤ አባላት የተወያዩባቸዉ ሲሆን፤ ማህበሩ በአመታዊ የስራ ክንዉኑ ያሳካቸዉን ተግባራት አድንቀዋል፡፡ በቀጣዩም አዲስ የስራ ዘመን ሊሻሻሉ እና ለካተቱ የሚገባቸዉን ሀሳቦች በማንሳት ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል፡፡
ማህበሩ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃውን ሁለት የጠቅላላ ጉባኤ አመራር አባላትን ለማስመረጥ የአስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም ምርጫ አካሂዷል፡፡ በዚህ መሰረት ወ/ሮ ዮዲት ሽፈራው፣ አቶ አለማየሁ አያሌው እና አቶ ሽመልስ ተሊላ በእጩነት ቀርበዋል፡፡ ከተመረጡት ውስጥ አቶ አለማየሁ አያሌው እና አቶ ሽመልስ ተሊላ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት በድጋሚ እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡